ረቡዕ ነሃሴ 30/2010 ዓ.ም ( ኣባይ ኤፍ ኤም )
ለ2011 በጀት ዓመት ምሩቅ ወጣቶች የመስኖ ፕሮግራም ይጀምራል፡፡
በ2011 በጀት ዓመት በፓይለት ደረጃ የ50 ሺህ ሄክታር ዘመናዊ የመስኖ እርሻዎችን እንዲያለሙ ለተማሩ ወጣቶች የመስኖ ልማት ፕሮግራም እንደሚጀመር የወሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ፕሮግራሙ እየተከሰተ ያለውን ሥራ አጥነት ለመቅረፍ በተለይም የመስኖ ውሃ ፤ መሬትና ቴክኖሎጂ በማቅረብ በተቀናጀ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት የተደራጁ ምሩቅ ወጣቶችን ተሳታፊ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
የመስኖ ልማቱ በተለያዩ ግድቦች ተይዞ ያለውን የከርሰ ምድር ውሃ በመጠቀም በየአቅራቢያው የሚገኙ መሬቶችን የተወሰነውን ለዚሁ ዓላማ እንዲውል ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን በዚህም ዘመናዊ ንግድ ተኮር የግብርና ልማት ሥራዎች ይከናወናሉ ተብሏል፡፡ የመስኖ ስራው የሚተገበረው ወጣቶችን በኢንተርፕራይዞች በማደራጀት ሲሆን አንድ ኢንተርፕራይዝ 12 የተለያዩ ሙያ ያላቸው ወጣቶችን ይይዛል፡፡ በአንድ ኢንተርፕራይዝ ስር 100 መካከለኛ ባለሙያዎችና የጉልበት ሠራተኞች ተቀጥረው ይሠራሉ ተብሎ ይታሰባል እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዘገባ፡፡
በ50 ሺህ ሄክታር ላይ 1000 ቡድኖች የሚደራጁ ሲሆን 12,000 ተመራቂ ወጣቶችን የያዘ ኢንቨስተሮችን መፍጠር የሚያስችል ሲሆን በዚህም በአጠቃላይ ለ112,000 ዜጎች የሥራ እድል ፈጥራል ተብሎ ይታመናል፡፡
በመስኖ ልማቱ የሚደራጁት አባላት ዕድሜያቸው 18 አስከ 29 የሆኑ ወጣቶች ሲሆኑ ከሚደራጁት መካከል 50 በመቶ ወጣት ሴቶች ይሆናሉ ተብሏል። በተጨማሪም አካል ጉዳተኞች በሚያሟሉት ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ይበረታታሉ።
በፕሮጀክቱ በተለይም በአካባቢው ለሚገኙ ወጣቶች ቅድሚያ እንደሚሰጥና በተጨማሪም በፕሮጀክቱ አካባቢ መስፈርቱንና መርሆዎችን የሚያሟሉ ወጣቶች ከሌሉ በክልል ላሉ ወጣቶች እና ለሌሎች ክልሎች እንደቅደም ተከተል ዕድሉ የሚሰጥ ይሆናል። ይህንኑ የሚያስፈፅም ለውሃ ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነ የፕሮግራም ዳይሬክቶሬት እንደሚቋቋምና በሂደት የፕሮግራም ዳይሬክቶሬቱ ወደ ኤጀንሲ ከፍ እንደሚል ታሳቢ መደረጉን የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከፌደራል መስሪያ ቤቶች እና ከክልል መስተዳደሮች በመውጣጣት በሚቋቋመው የስትሪንግ ኮሚቴ እንደሚደገፍ የገለፀው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአደረጃጀት ሁኔታው የሚከናወነው ከክልሎች ጋር መሆኑንና በቀጣይ ወራት እንደሚያስታወቅ ገልጿል፡፡
ለመስኖ ፕሮጀክቱ ልማት ብር 1 ቢሊዮን በመጀመሪያው ዓመት ከመንግስት ተመድቧል፡፡
ምንጭ፡- የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚ/ር ህዝብ ግንኙነት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *