ዓርብ ነሃሴ 25/2010 ዓ.ም ( ዓባይ ኤፍ ኤም )
በደቡብ ክልል ዜጎችን ወደ ቀድሞ የመኖሪያ ቦታቸው የመመለሱ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ከደቡብ ክልልና ከአጎራባች አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ነበሩበት የመኖሪያ አካባቢያቸው የመመለሱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ አደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
በክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎች ብዛት በአጠቃላይ እስከ 1.2 ሚሊየን ህዝብ መድረሱን ያስታወቀው ምክር ቤቱ ከእነዚህ ውስጥም በጌድኦ ዞን 623 ሺህ 228 ህዝብ ተፈናቅሎ በመጠለያ ጣቢያዎች የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ግዜ ከ319 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደየመኖሪያ ቀያቸው መመለሳቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን ከበደ ገልፀዋል፡፡ ይህም ማለት ከዞኑ ተፈናቃዮች 52 በመቶ ያህል መሆኑ ነው፡፡
በተመሳሳይም ከሀዋሳ ከተማ ተፈናቅለው የነበሩ 3ሺህ 250 ዜጎች ወደየመኖሪያ ቤታቸው እንዲመለሱ ሲደረግ ቀሪዎቹ በሀዋሳ ፣ በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን በአማሮና በጉጂ ወረዳዎች ፣ በሲዳማ ዞንና በምዕራብ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን አስከ ነሐሴ 30/ 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ወደ ቀድሞው ቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ሰብሳቢው ጠቅሰዋል፡፡
የተፈጠሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች በየቀየው እርቅ እንዲፈፀም እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደነበሩበት ቦታ ለመመለስና አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረግ ክልላዊ የሀብት አሰባሰብ ግብረ-ኃይል ተቋቋሞ 1ቢሊየን ብር በማሰባሰብ ዜጎችን ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ምንጭ፡- የደቡብ ብ/ብ/ህ/ኮምንኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *