ግንቦት 30 /09/10 ዓ.ም ( ዓባይ ኤፍ ኤም )
ለ2011 በጀት አመት የተመደበው 346.9 ቢሊዮን ብር የክልሎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሊሆን ይገባዋል ሲል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ፣፡
ምክር ቤቱ ባካሄደው 30ኛ መደበኛ ስብሰባው ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር በቀረበለት የ2011 በጀት አመት ረቂቅ የበጀት አዋጅ ላይ ተወያይቶ አዋጁን ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም ተከስተ ረቂቅ በጀቱን ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ለ2011 በጀት ተደግፎ የቀረበው የፌደራል መንግስት በጀት 346.9 ቢሊዮን ብር እንደሆነና ከ2010 በጀት ጋር ሲነጻጸር የ3.6 በመቶ እድገት ማሳየቱን አንስተው ከዚህም ውስጥ 39.1 በመቶው የክልሎች ድርሻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በጀቱ ሲደለደል የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ቀሪ ወራትንና የክልሎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ግምት ውስጥ ያስገባ እንደሆነና በጀቱም ከሀገር ውስጥ ገቢ እንዲሁም ከውጭ አገር እርዳታና ብድር እንደሚሸፈን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
አገራችን አስካሁን እድገት ያስመዘገበችባቸው ዘርፎች አገልግሎትና ኮንስትራክሽን እንደሆኑ ሚኒስትሩ ጠቁመው ነገር ግን የኢኮኖሚ እድገቱን ዘላቂና ተወዳዳሪ ከማድረግ አንፃር በቂ ስላልሆኑ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመንና ኢንዱስትሪውን ማሳደግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የኤክስፖርት ንግድን ማሳደግ ለፈጣን የኢኮኖሚ እድገት መሰረት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ የአምራች ዘርፉን የማምረት አቅም ለማሳደግና አሟጦ ለመጠቀም ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል፡፡
ለታክስ ገቢ መቀነስ ዋናው ምክንያት የመንግስት ትኩረት ማነስ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ ታክስን ትኩረት ሰጥቶ መሰብሰብ ካልተቻለ በየደረጃው ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች መመለስ ስለማይቻል የግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱን ማዋቅር አቅም መገንባትና ሃብትን አሟጦ መጠቀም የሚያስችል አሰራር መከተል የግድ ይለናል ብለዋል፡፡
በጀትን በግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ ማስተዳደርና የፌደራል ዋና ኦዲተር የሚሰጠውን የኦዲት አስተያየት ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ የምክር ቤት አባላትም የተለመደ የክትትልና ቁጥጥር ስራቸውን የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉና የተመደበው በጀት ለታለመለት አላማ እንዲውል ለማድረግ ተቀናጅተን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱም ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል ያላቸውን ጥያቄዎች ጨምሮ የበጀት ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር እይታ ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡
ምንጭ፡- የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *