ግንቦት 30/09/10 ( ዓባይ ኤፍ ኤም )
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፉት ቀናት ያወጣውን መግለጫ በተለይም የኢትዮ -ኤርትራን ጉዳይ በተመለከተ ዓረና ትግራይ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
ከዓረና ትግራይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ፡-
የኢህአዴግ ስራ አሰፈፃሚ ኮሚቴ በ28/9/10 ዓ.ም ባሳለፈው አስደንጋጭና አሳፋሪ ውሳኔ የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል። በተጨማሪም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ለኤርትራ መንግስት ጥሪ አቅርቧል።
ዓረና/መድረክ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጉዳይ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ደማቸው ያፈሰሱበትና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሂወታቸው የገበሩበት ነው። ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ወገኖቻችንን ለስደትና ለሞት የዳረገ ከመሆኑም በተጨማሪ ትልቅ የሀገር የፀጥታና የደህንነት ጉዳይ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። በአጭሩ የሻዕቢያ ወረራ ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ሉዓላዊነታቸው ለማስከበር እንደንብ ተግተልትለው የወጡበትና የአንድነት ሀወልታቸው በደማቸው ታሪክ የሰሩበት ነው።
ዓረና/መድረክ ይህንን ትልቅ ሀገራዊና ህዝባዊ አጀንዳ ህዝብ ሳይመክርበትና ሳይወያይበት በንዲህ መልኩ ይፋ መደረጉ የኢህአዴግ አንባገነናዊ ባህሪ አሁንም መቀጠሉና በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች እንኳ ፖለቲከኞችና ምሁራን እንዲሁም ህዝብ ለማሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው በግልፅ ያሳየ ነው።
ዓረና መድረኽ ይህንን የአገር ሉዓላዊነትን በቀጥታ የሚፃረር ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ እንዲቃወመው ጥሪ ያደርጋል። ዓረና/መድረክ የአልጀርስ ስምምነት በሻዕቢያ የፈረሰና የተጣሰ በመሆኑ ሕጋዊነቱ ያበቃለትና ፈፅሞ ወደ ኋላ የማይመለስ ነው።
ዓረና/መድረኽ የኢህአዴግ ውሳኔ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚነካ ከመሆኑ ባሻገር የለየለት የሀገር ክህደት መሆኑ በፅኑ እንደሚያወግዝ ይገልፃል። የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጉዳይ ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳ እንደመሆኑ መጠን በአንድ ፈላጭ ቆራጭ ፓርቲ የሚያልቅ ሳይሆን ሁሉም ህዝብ ተሳታፊ ሆኖ ውሳኔ እንዲሰጥበት ይጠይቃል።
ዓረና ይህንን የሀገር ክህደት ለማክሸፍ ከመላ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ሀገር ወዳድ ወገኖቻችን በጋራ እንደሚሰራ እያስታወቀ በቅርቡ በመላ ትግራይ ታላላቅ ህዝባዊ ስብሰባዎችና የተቃውሞ ሰልፎች እንደሚጠራ ያስታውቃል።
በመሆኑም መላው የሀገራችን ህዝብ እንደወትሮው ሁሉ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ዘብ እንዲቆም የአክብሮት ጥሪያችን እናቀርባለን።
ምንጭ፡- ዓረና ትግራይ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *