ግንቦት 15/09/10ዓ.ም ( ዓባይ ኤፍ ኤም )
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር አመራሮች አዲስ አበባ ገቡ፡፡
መንግስት በአገሪቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የፖለቲካ ትግሉ እንዲካሄድ በማሰብ ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ የኦሮሞ ዴሞክራያዊ ግንባር (ኦዴግ) ዛሬ ማለዳ ላይ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ አቶ አባ ዱላ ገመዳና የኢፌዴሪ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ተቀብለዋቸዋል፡፡
የኦፌግ ፕሬዚዳንት አቶ ሌንጮ ለታ መንግስት ባደረገው ጥሪ መሰረት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ትግሉን ለማድረግ የሚፈልጉ ሲሆን ሌሎችም በትጥቅ ትግሉ ውስጥ ላሉ የፖለቲካ ድርጅቶችም ከትጥቅ ትግሉ ወጥተው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ትግላቸውን ቢያካሂዱ የተሻለ ነው ብለዋል፡፡
የኢፌዴሪ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው፤ ኦዴግ ሰላማዊ፣ ህጋዊና ህገ መንግስታዊ ትግሉን በመቀላቀል የፖለቲካ ዓላማውን በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ የመንግስት ጥሪ ተቀብሎ ወደ አገር ቤት መግባቱን ይመሰገናል ብለዋል፡፡
ከግንባሩ ጋር በቀጣይ የሚደረገው ድርድር ህገ መንግስቱን መሰረት ያደረገ አካሄድን የተከተለ እንደሚሆንም ጠቁመው ሌሎች የፖለቲካ ተደራዳሪ ፓርቲዎችም ይህንን መንገድ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የቀድሞው የኦነግ ሊቀመንበር የነበሩት የአሁኑ የኦዴግ ምክትል ሊቀመንበሩ ዶክተር ዲማ ነገዎ፤ ከመንግስት ጋር ድርድር ማድረግ የጀመሩት ከአምስት ዓመታት በፊት ጀምሮ መሆኑን ጠቁመው ሁኔታዎች በአሁኑ ሰዓት ምቹ በመሆናቸው ወደ አገር ቤት ገብተው ለመንቀሳቀስ መወሰኛቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህን አስመልክቶ በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ከመንግስት ጋር እንደሚወያዩ የሚጠበቅ ሲሆን ከሚነጋገሩበት ጉዳይ አንዱ በአገሪቱ ባለፈው ጊዜ ጠብቦ የነበረው የፖለቲካ ምህዳር መስፋትን በተመለከተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አገር ቤት የገቡ የግንባሩ አባላት ፡አቶ ሌንጮ ለታ ፕሬዚደንት ፤ዶ/ር ዲማ ነገዎ ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር በያን አሶባ ፤ አቶሌንጮ ባቲ ና ዶ/ር ሐሰን ሑሴን ናቸው፡፡
ምንጭ፡-የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *