ግንቦት 14/2010 ዓ/ም ( ዓባይ ኤፍ ኤም )

የትግራይ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ገብረመስቀል ካህሳይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት በክልሉ የሚሰጡትን ክልላዊና ብሔራዊ ፈተናዎች የተሳካ ለማድረግ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።
በተለይ በአንዳንድ ተማሪዎች ሊፈጸም የሚችለውን የፈተና ኩረጃ ለማስቀረት ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው የፈተና ሂደቱን ስኬታማ ለማድረግ ከ10 ሺህ በላይ ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች ፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።
”ኩረጃ ሊወገዝ ይገባል፤ ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን ህዝብና አገርንም የሚያጠፋ የሙስና ተግባር ነው” ያሉት ዶ/ር ገ/መሰስቀል ኩረጃን ለማስቀረት ከወላጆች ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
የ8ኛ ፣ 10ኛ እና 12ኛ ክፍል ፈተናዎች በክልሉ በተዘጋጁ 400 የመፈተኛ ጣቢያዎች እንደሚሰጡና በሦስቱም ፈተናዎች በአጠቃላይ 240 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች እንደሚፈተኑም ዶክተር ገብረመስቀል አስረድተው ዘንድሮ ለአገርና ክልል አቀፍ ፈተና የሚቀርቡ ተማሪዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተፈታኞች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በ22ሺህ ብልጫ አሳይቷል።
በክልሉ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቶች ቁጥር በመጨመሩ ለተፈታኝ ተማሪዎች ቁጥር መጨመር ዋነኛ ምክናያት መሆኑንም ጠቁመዋል ፡፡
እንደዶክተር ገብረመስቀለ ገለጻ፣ የሮመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ በተያዘው ግንቦት ወር መጨረሻ በክልል ደረጃ ሊሰጥ የነበረው የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ተራዝሞ ከሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት እንዲሰጥ ተወስኗል።
ምንጭ፡- ኢ ዜ አ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *