ግንቦት 8/09/10 ዓ.ም ( ዓባይ ኤፍ ኤም )

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚንስትር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራሮች ጋር ግንቦት 6/2010 ዓ.ም. በተቋሙ ተገኝተው ትውውቅ አድርገዋል፡፡ በዚሁ የትውውቅ መድረክ የኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ የሚገኝበትን ሁኔታ የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም እና የኢንዱስትሪውን አጀማመር ፣ እድገት፣ ፈተናዎች እንዲሁም ተስፋዎች የሚገልጽ ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል፡፡
ሚኒስትሩ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ቀሪ ዓመታት በስኳር ልማት ዘርፍ የተጀመሩ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን ለማሳካት ሚኒስቴር መ/ቤቱ በተቋማዊ የአመራር ሥርዓት ግንባታ ፤ በአገር ውስጥ ፋይናንስና በውጭ ምንዛሪ ግኝት ፣ የውጭ ገበያና በጋራ የሚያለሙ አጋሮችን በማፈላለግ እንዲሁም የክልል መንግሥታት የዘርፉን ልማት እንዲደግፉ በማድረግ ረገድ የበኩሉን ኃላፊነት እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡
በኮርፖሬሽኑ በኩል ከሁሉም በላይ የውስጥ ችግሮችን ለመፍታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ የገለጹት አምባሳደር ተሾመ የኮርፖሬሽኑ የውስጥ ችግር ከተፈታ ውጫዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ይቻላል ካሉ በኋላ ይህንን በመተግበር በመጪዎቹ ዓመታት ማምረት ያልጀመሩ አዳዲስ ስኳር ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ እንዲሁም ወደ ምርት ገብተው ነገር ግን በሙሉ አቅማቸው መስራት ያልጀመሩትን ደግሞ ሙሉ አቅማቸው ላይ እንዲደርሱ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በዘርፉ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ግልጽ የሆነና ተጠያቂነት ያለው የአሠራር ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ ቅድሚያ ትኩረት ከሚሰጠው የኮርፖሬሽኑ ተልዕኮ ውስጥ ዋንኛው መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ለአሠራር ምቹ በሚሆን መልክ የተቋሙን አደረጃጀት በመፈተሽና የሰው ኃይል ልማት ላይ ያለውን ክፍተት በመለየት በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት አቅምን መገንባት እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት በልማቱ አካባቢ የሚገኘው ማህበረሰብ “ልማቱ የእኔ ነው” ብሎ በባለቤትነት መንፈስ እንዲንቀሳቀስና ልማቱን እንዲደግፍ ማድረግ ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ይህ ግን ኮርፖሬሽኑ ሊያሳካ የተሰጠውን የቢዝነስ ተልዕኮ በሚያዛባ ደረጃ ሚዛኑን ስቶ መፈጸም እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል እሳቸው የሚመሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ጨምሮ በዘርፉ ከተሰማሩ ሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር አገራዊ ተልዕኮን ለማሳካት ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ በማሳሰብ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *