ግንቦት 7/09/10 ( ዓባይ ኤፍ ኤም )

በኢትዮጵያ ጤና ኢንስትትዮት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ኤባ አባተ በዛሬው ዕለት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ ለመገናኛ ባለሙያዎች በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እዳስታወቁት በሽታውን ለመከላከል እንዲቻል ከፌዴራል እስከ ወረዳ ባሉ በሁሉም የአስተዳደር መዋቅሮች የኢቦላ መከላከል ቅድመ ዝግጅት አስተባባሪ ግብረሀይል መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡
ዋናው ዳይሬክተር አያይዘውም በሽታው ሊከሰትባቸው ይችላሉ ተብለው የሚገመቱትን ቦታዎች በመለየት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ በአለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎችና በዋና ዋና የድንበር በሮች ላይ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱ ገልፀዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የበረራ ጣቢያዎች በሚሰጡት በሁለቱም ማለትም በቦሌ እና በድሬዳዋ አየር ማረፊያዎች በሽታው ከተከሰተበት ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና አካባቢ አገራት እንዲሁም ወደ እነዚህ ሀገራት በቅርቡ ተጉዘው የሚያውቁ የአየር መንገዱ ደንበኞች ላይ ለበሽታቸው መጋለጣቸውን በተመለከተ የሰውነት ሙቀት በመለካት የመለየት ምርመራ ማድረግ ተጀምሯል፡፡ በበሽታው የተጠረጠሩ የአየር መንገድ ተጓዞችም የሚቆጡበት ማዕከል በአየር መንገዶቹ ውስጥ መደራጀቱን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዲሞክቲክ ሪፕብሊክ ኮንጎ ኢቦላ በተባለ ቫይረስ አማካኝነት የሚተላለፈው የበሽታ ወረርሽኝ ከሚያዝያ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ዳግም እንደተከሰተ ይታወቃል፡፡ ደቡብ ሱዳን የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የኢትዮጵያ የጋራ አዋሳኝ በመሆኗ እና በየብስ ትራንስፓርት የሰዎች እንቅስቃሴ ሊኖር በመቻሉ እንዲሁም ከኡጋንዳ እና ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ደግሞ የቀጥታ የአየር ትራንስፓርት ግንኙት ያለን በመሆኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራውን መጀመሩ አስስፈላጊ መሆኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተወስቷል፡፡ በሽታው ድንበር ዘለልና በከፍተኛ ደረጃ በወረርሽኝ መልክ የሚዛመት በመሆኑ በሽታው እንዳይከሰት ቀድሞ መዘጋጀትና ቅድመ መከላከል ዝግጅት ማድረጉ አስፈላጊ በመሆኑ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ቀድሞ መጀመሩን ዋና ዳይሬክተር አስተረድተዋል፡፡
ምንጭ፡- የጤና ጥበቃ ሚ/ር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *