የካቲት 5፣ 2010

አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የሰባት ተጠርጣሪዎች ክስ ተቋረጠ።

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወሰነው መሰረት በተከታታይ በሁከትና ብጥብጥ፣ በሽብር እንዲሁም በሀይማኖት አክራሪነት ክስ የተመሰረተባቸው እና ቅጣት የተወሰነባቸው ግለሰቦች ላይ ክስ የማቋረጥ እና ይቅርታ የማድረግ ተግባር ሲከናወን መቆየቱ ይታወቃል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፀው፥ ይህንን ተከታታይነት በመቀጠል በሀገሪቱ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ ግለሰቦች ክስ እንዲቋረጥ መንግስት ወስኗል።

በዚህም መሰረት አቶ በቀለ ገርባ፣ ጉርሜሳ አያና፣ አዲሱ ቡላላ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ ጌቱ ጋሩማ፣ ተስፋዬ ሊበን እና በየነ ሩዳ ክሳቸው እንዲቋረጥ ተወስኗል።

ነገር ግን ተጠርጣሪዎቹ ችሎት ፊት ቀርበው ጉዳያቸውን በሚከታተሉበት ጊዜ ባሳይዋቸው ችሎት የመድፈር እና ህግ የመጣስ ተግባራት ምክንያት ጉዳዩን የሚመለከተው ፍርድ ቤት በእያንዳንዳቸው የአንድ ዓመት እና የስድስት ወር ቅጣት መበየኑ ይታወቃል።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ በዚህ ምክንያት ጉዳያቸው በፌደራል የይቅርታ ቦርድ እንዲታይ የተወሰነ መሆኑን እና ጉዳዩም ለሀገሪቱ ርእሰ ብሄር ቀርቦ ሲፀድቅ ወደ ህብረተሰቡ እንደሚቀላቀሉ ነው ያስታወቀው።

ምንጭ :- ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *