( ጥር 23-2010 )

የአማራ ክልላዊ መንግስት  ለሁለት ሺህ 905 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

የአማራ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት  ዛሬ ከሰዓት በኋላ ባካሄደው ስብስባ ለሁለት ሺህ 905 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ እንዲደረግላቸው መወሱኑን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።

ይቅርታ ከተደረገላቸው መካከልም  62 ሴት ታራሚዎች ይገኙበታል፡፡

የቢሮው ኃላፊና ጠቅላይ አቃቢ ህግ  አቶ ፍርዴ ቸሩ ማምሻውን እንዳስታወቁት የክልሉ መንግስት ለታራሚዎቹ  ይቅርታውን ያደረገው  በማረሚያ ቤት ቆይታቸው  በሰሩት ወንጀል ተፀፅተው  የበደሉትን ህዝብ ለመካስ ዝግጁ የሆኑትን ነው፡፡

ታራሚዎቹም ይቅርታ እንዲደረግላቸው በመጠየቃቸውና  መስፈርቱን አሟልተው በመገኘታቸው የክልሉ መንግስት ይቅርታ እንዲደረግላቸው ወስኗል፡፡

“በይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑትም በነብስ ግድያና ሙከራ፣ በስርቆት ፣ በማጭበርበርና መሰል ወንጀሎች በፍርድ ውሳኔ ተሰጥቷቸው በትክክል የባህሪ ለውጥ ያስመዘገቡ ናቸው “ብለዋል።

ይቅርታ የተደረገላቸው እነዚህ ታራሚዎች  ከእድሜ ልክ  እስከ አንድ ዓመት  የእስራት ቅጣት በፍርድ ቤት ውሳኔ ተላልፎባቸው የነበሩ መሆናቸውን የፍትህ ቢሮው ኃላፊ ጠቅሰዋል፡፡

ይቅርታ ሲደረግም ታራሚዎች አድሏዊ አሰራር እንዳይፈፀምባቸው ለማድረግም የክልሉ ይቅርታ ቦርድ ክትትል በማድረግ የተለዩ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ሆኖም ይቅርታው  በሙስና፣ በአስገድዶ መድፈር፣በህገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር፣ በዘር ማጥፋትና መሰል ወንጀሎች የተሳታፊ የሆኑትን እንደማይመለከት ነው   አቶ ፍርዴ ያስታወቁት፡፡

በክልሉ ባለፉት ጊዜያት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በህግ ጥላ ስር ውለው ጉዳያቸው ይታይ የነበሩ 598 ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋርጦ ዛሬ እንዲፈቱ መደረጉንም አስታውቀዋል።

ምንጭ

(ኢዜአ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *