(ጥር 09   2010 )

የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ የፈረንጆች 2018 ዓመት የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ።

30ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ ሲከፈት የሊቀመንበርነት ኋላፊነቱን ከጊኒው ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ተረክበዋል።

ፖል ካጋሜ ባደረጉት ንግግር ቀደም ሲል ህብረቱን በሊቀመንበርነት ካገለገሉ መሪዎች ጋር በቅርበት ይሰሩ በነበረበት ወቅት የቀሰሙትን ሰፊ ልምድና እውቀት በመተግበር የተሻለ ስራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቀደምት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና የአፍሪካ ህብረት መሪዎች አህጉሪቱን ወደ ብልጽግና ለመጓዝ የሚያስችለውን መንገድ መጥረጋቸውን አስታውሰዋል።

ህብረቱ የጣለባቸውን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት ከሁሉም አካላት ጋር በትብብር በመስራት ለውጤት እንደሚተጉ ገልጸዋል።

የአፍሪካን  ችግር በመለየት እየተሰራ ያለው ስራ ወደ በለጸገ አህጉርነት የሚያሸጋግር እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ካጋሜ ቀሪ ስራዎች በርካታ በመሆናቸው በመተባበር ለመስራት መነሳሳት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

አፍሪካን በቋሚነት ወደ ኋላ ከሚጎትተው ችግር ለማውጣት ሩጫ መጀመሩን አመልክተው የኢኮኖሚ እድገቱን ለማፋጠን ወጥነት ያለው አህጉራዊ የገበያ ስርዓት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

መሰረተ ልማትን ለማቀናጀት የተቀናጀ አህጉራዊ  ገበያ ያስፈልገናል ይህም ለኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ  ጠቃሚ ነው ብለዋል።

ብቻውን ሆኖ ያደገ የለም ያሉት ፕሬዝዳንት ካጋሜ ተቀናጅተን በመስራት አብረን በእድገት ጎዳና እንዘልቃለን ብለዋል።

አፍሪካ የራሷ የሆነ እሴትና ጥንካሬ ያላት በመሆኑ ህብረት በመፍጠር ለውጥ ለማምጣት አህጉራዊ አንድነቱን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አንድነት የሁሉም ለውጦች መነሻ ነጥብ ሊሆን ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንት ካጋሜ እዚህ ላይ በመመስረት ማቀድና ስትራቴጂ መንደፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ህብረቱ በዚህ የመሪዎች መደበኛ ጉባዔ በአጀንዳ 2063፣ ወጥ የአፍሪካ አየር ትራንስፖርት ገበያ፣ በሰዎች ከቦታ ቦታ በነጻ መዘዋወር፣ በህብረቱ የፋይናንስ ሪፎርምና በሙስና ዙሪያ እንደሚመክር ጠቁመዋል።

ለምሁራን፣ ለወጣቶችና ለሴቶች ባስተላለፉት መልእክት ህብረቱ ያለነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ለውጥ ሊያመጣ ስለማይችል በመቀራረብ ለመስራት ዝግጁነት እንዳለ ተናግረዋል።

የአፍሪካ መሪዎች ዋና ስራ እያንዳንዱ የአፍሪካ ትውልድ ቀደም ሲል ከነበረው ህይወት የተሻለ ህይወት እንዲመራ ማድረግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ጋር በጋራ እንዲሰሩ የሊቢያ ፕሬዝዳንት ቫይስ ኤልሳራጅ፣ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ፣ የኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዴኒሳሶ ንጉዌሶ እና የጊኒ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ከየአካባቢው ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው ተሰይመዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *