(ጥር 21-2010)

የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መሪዎች የሶስትዮሽ ስብሰባ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር እና የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ ኤል ሲሲ በስብሰባው ላይ ተካፍለዋል።

ሶስቱ መሪዎች በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው 30ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ተገናኝተው የመከሩት።

መሪዎቹ በነበራቸው ቆይታም በሶስቱ ሀገራት የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ውይይቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ፣ ግብፅጽና ሱዳን በሶስትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

መሪዎቹ በሶስቱ ሀገሮች መካከል የተፈጠረውን ወንድማማችነት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እንደሚያስፈልግ መስማማታቸውንም ገልፀዋል።

ሶስቱ አገሮች እንደ አንድ በመቆም የሚያጋጥሟቸው ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መወሰናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በሰጡት መግለጫም፥ ሶስቱም ሀገራት የጋራ ጉዳያቸውን እንደ ሌላ የተናጠል ሀገራት ሳይሆን እንደ አንድ ሀገር ይመለከቱታል ብለዋል።

በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ድግብን በተመለከተ በግድቡ ዙሪያ ሁሉንም ሀገራት ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በጋራ መንፈስ ለመስራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

የሀገራቱ የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮችም በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና በግብፅ በኩል የሚነሱ ጉዳዮችን በማጣራት እና ጉዳዮቹን ለመፍታት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጥናት አካሂደው ለመሪዎቹ እንዲያቀርቡ መስማማታቸውን ዶክተር ወርቅነህ አስታውቀዋል።

የሶስቱ ሀገራት መሪዎች በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ጥናቱን የሚያካሂዱት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሀገራቱን ህዝቦች ጥቅም ማእከል ያደረጉ ስራዎችን እንዲያከናውኑ አሳስበዋል ብለዋል።

በዓመት አንድ ጊዜም በመሪዎች ደረጃ እየተገናኙ በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገርና አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥም ሶስቱ መሪዎች ተስማምተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪ፥ ሶስቱም ሀገራት የጋራ የመሰረተ ልማት ፈንድ ለማቋቋም እንደተስማሙ አስታውቀዋል።

የመሰረተ ልማት ፈንዱ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅን የሚያስተሳስር በመሆኑ የህዝብ ለህዝብ እና የመተማመን ስሜትን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል ብለዋል።

የፈንዱንም በጀት ሶስቱም ሀገራት እኩል እንደሚጋሩትም አቶ መለስ አብራርተዋል።

የመሪዎቹ ውይይት በአጠቃላይ ስኬታማ እንደነበረም ነው ያነሱት።

ምንጭ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *