( ጥር 21-2010 )

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሁሉን አቀፍ የአፍሪካ የግብርና ልማት መርኃ ግብር አፈጻጸም ሪፖርትን ዛሬ ከቀትር በኋላ ለአፍሪካ ህብረት መሪዎች ያቀርባሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ንጋት ላይ ሁሉን አቀፍ የአፍሪካ የግብርና ልማት መርኃ ግብር ያካሄደውን ስብሰባ በሊቀ መንበርነት መርተዋል

በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩትም የአህጉሪቷ የግብርና ዘርፍ በርካታ የሥራ እድል የሚፈጠርበትና በአገሪቱ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት አስፈላጊነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም።

ለዚህ ደግሞ ከጥቂት ዓመታት ጀምሮ በጉዳዩ ላይ በአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ አማካኝነት ጠቃሚ ውይይቶችና ድርድሮች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል፤ አንዳንድ አገራትም የሰሩት ሥራ በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን አንስተዋል።

የእነዚህንም አገራት ተሞክሮ በመቀመር ወደ ኋላ የቀሩት አገራት ወደ ፊት መምጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ያም ሆኖ በዘርፉ ላይ  አሁንም ክፍተት መኖሩን ጠቁመው ለዚህም የአፍሪካ አገራት በጋራ ብንሰራ ውጤታማ ልንሆን የምንችልባቸው አጋጣሚዎች አሉ ብለዋል።

እንዲያም ሆኖ አገራት በግብርና ዘርፍ ያገኙትን ውጤት ለሌሎች አገራት በማካፈል የአህጉሪቱን የግብርና ዘርፍ ተሃድሶ ማሳካት አለባቸው ብለዋል።

ለተሃድሶው መሳካት የአፍሪካ አገራት ቁርጠኛ አቋም ሊኖራቸው እንደሚገባም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳሰቡት።

ከዚህ በኋላ በዘርፉ ዘላቂ እድገት ለማምጣት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች በአህጉሪቱ ግብርና ሴክተር ላይ እንዲመክሩ ይደረጋልም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ ከቀትር በኋላ ሁሉን አቀፍ የአፍሪካ የግብርና ልማት መርኃ ግብር ዝርዝር አፈጻጸምን አስመልክቶ ለ30ኛው የመሪዎች ምልዓተ-ጉባኤ ሪፖርት ያቀርባሉ ተብሏል።

ምንጭ

(ኢዜአ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *