( ጥር 21-2010 )

የመንግሥታቱ ድርጅት በአፍሪካ ያሰማራውን የሰላም አስከባሪ ሰራዊት መልሶ ለማዋቀር እቅድ እንዳለው የድርጅቱ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ ገለጹ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ያለውን ግንኙነት በተለመከተ ዋና ጸኃፊው ትላንት ማምሻውን መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ጸኃፊው በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በመንግሥታቱ ደርጅት ሥር የሚንቀሳቀስ በርካታ የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በአፍሪካ ይገኛል።

ይሁን እንጂ ሰራዊቱ በተመደበበት አካባቢ እስካሁን የፖለቲካ መፍትሄ አለመገኘቱን ጠቁመው በርካታ የሰራዊቱ አባላትም ለጉዳት መዳረጋቸውን አንስተዋል።

ያም ሆኖ የሰላም አስከባሪ ሰራዊቱን ማንሳት ሁነኛ መፍትሄ አይደለም፤ እንዲያውም ለአገራቱ ውድቀትን ሊያስከትል ይችላል በማለት ነው ግምታቸውን የተናገሩት።

ድርጅቱም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፤ ወታደር ከሚያዋጡ አገራትና የገንዘብ ድጋፍ ከሚያቀርቡ አካላት ጋር ይወያያል ብለዋል።

በዚህም የሰላም አስከባሪ ጦሩ መልሶ እንዲቋቋም ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ዋና ጸኃፊው አረጋግጠዋል።

ይህ ደግሞ በተለይም በአፍሪካ ከፍተኛ የሰላም አስከባሪ ጦር በሚገኝባቸው በሶማሊያ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በማሊ፣ በደቡብ ሱዳንና በማዕከላዊ አፍሪካ ላይ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።

ይህም የሆነው የሰላም አስከባሪ ሰራዊቱ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ አንዲያተኩር በማድረግ የፖለቲካ መፍትሄ ለማምጣትና ለዜጎች የተሻለ ከለላ ለመስጠት መሆኑን አንስተዋል።

በተጓዳኝም የሰላም አስከባሪ ሰራዊቱ ለተልዕኮው ዝግጁ፣ በሚገባ የታጠቀና ለችግሮች አስቀድሞ ምላሽ አንዲሰጥ በማስቻል ሰላምን እንዲያሰፍን ያስችላል ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም በአፍሪካ ያለው የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ተልዕኮውን ለመወጣት የሚያስችለውን የገንዘብ ድጋፍ በዘላቂነት ለማፈላለግ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በሶማሊያ የተሰማራው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ሰራዊት (አሚሶም) የሰራው ሥራ የሚያበረታታ ቢሆንም ተጨባጭ የገንዘብ ምንጭ አለመኖሩን ለአብነት አንስተዋል።

በተጓዳኝም የመንግሥታቱ ድርጅትና የአፍሪካ ኅብረት በጋራ በመሆን በአህጉሪቷ ሽብርተኝነትን ለመመከት በትጋት እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በቅርቡ በመንግሥታቱ ድርጅትና በአፍሪካ ኅብረት መካከል የተደረሰው የስትራቴጂክ አጋርነት ሥምምነት ምሳሌ ሊሆን አንደሚችል ጠቁመዋል።።

ከቀናት በፊት የመንግሥታቱ ድርጅት የ2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳና የአፍሪካ ኅብረት የ2063 አጀንዳ ተጣጥመው እንዲተገበሩ ሥምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል።

የሁለቱን የልማት እቅዶች አፈጻጸምም በተመለከተ ከዚህ በኋላ በጋራ እንደሚሰራና የጋራ ግምገማ በማድረግ ለተግባራዊነቱ ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅትም በአፍሪካ የሚወጡት ሕጎችና ደንቦች ተፈጻሚ እንዲሆኑና በሰዎች ህይወት ላይ የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያመጡም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቀት የመንግሥታቱ ድርጅት ካሰማራቸው ዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በአፍሪካ አገራት የሚገኙ ናቸው።

ምንጭ

(ኢዜአ)

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *