(ጥር 2 – 2010)

የህግ የበላይነትንና ህገ መንግስታዊ የዜጎች መብትን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ህዝቡ እያደረገ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ጥሪ አቀረቡ።

ሚኒስትሩ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ በሃገሪቱ ተጥሎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተነሳ ወዲህ በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች ችግሮች መስታዋላቸውን አንስተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ይህን ለመቆጣጠርና ሁኔታውን ወደ ነበረበት ለመመለስ ብሄራዊ የደህንነትና የፀጥታ ምክር ቤት ተቋቁሞ ለአንድ ወር ከ15 ቀን ያከናወነውን ስራ ገምግሟል ብለዋል።

በዚህም በሃገሪቱ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተፈጠሩ ግጭቶችን፣ በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች የተፈጠሩ ግጭቶችንና አስተባባሪያቸው በማይታወቁ አካላት የተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎችን ገምግሟልም ነው ያሉት።

ሚኒስትሩ የፌደራልና የክልል የፀጥታ አካላትም በጋራ እቅድ አውጥተው በመንቀሳቀስ ያከናወኑትን አፈጻጸመ ላይ አተኩረው መግለጫቸውን ሰጥተዋል።

የፀጥታ ሃይሉ በአንዳንድ አካባቢዎች ታይተው የነበሩ ግጭቶችና ሁከቶችን ከማረጋጋት አንጻር በከፊል ውጤታማ ስራ ሰርቷልም ነው ያሉት ሚኒስትሩ በመግለጫቸው።

ከዚህ ባለፈም የዜጎችን በሰላም የመንቀሳቀስ መብትና ደህንነት የሚፈታተኑ ጉዳዮች አሁን ላይ በፀጥታ አካሉ እርምጃ መስተካከላቸውንም ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ አሁንም በአንዳንድ ኪስ ቦታዎች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶችን ሰንደቅ አላማ የያዙ ግለሰቦች የሚያካሂዷቸው ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚታዩም ጠቅሰዋል።

በትምህርት ተቋማት ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት ተቀርፏል ያሉት ሚኒስትሩ፥ አሁን ላይ መደበኛ የመማር ማስተማር ስራው ወደነበረበት መመለሱን አስረድተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ተሳታፊ ናቸው የተባሉ አካላት ጉዳይ በህግ እየታየ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውጤት ያላሟሉ ተማሪዎች መገኘታቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ እነዚህን ተማሪዎች በማጣራት ወደ ቤተሰቦቻቸው የመላክ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ ድንበሮች ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት ክልሎቹ በጠየቁት መሰረት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ግጭት ባለባቸው የክልሎቹ አካባቢዎች በመግባት ሁኔታውን ማስተካሉንም ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በሀገሪቱ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋትን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ የህገ ወጥ መሳሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሊገባ ሲል ተይዟል ብለዋል።

በዚህም ወደ አዲስ አበባ ሊገባ የነበረ 270 ክላሽንኮቭ፣ 200 ሺጉጥ፣ 65 ሺህ የክላሽ ጥይትና 1 ሺህ የመትረየስ ጥይት መያዙን ጠቅሰዋል።

መንግስት ህግና የህግ የበላይነትን ለማስፈን ለሚያደርገው ጥረትም ህዝቡ ተሳፍፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *