(ታህሳስ 25 – 2010)

የገናሌ ዳዋ ቁጥር 3 የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ሀይል ለማመንጨት የሚያስችሉ የኤሌክትሪካልና የመካኒካል ስራዎች መጠናቀቃቸውን ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታውቋል።

የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ግንባታ 94 በመቶ መጠናቀቁን ነው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ የተናገሩት።

የግድቡ ውሃ ማስተንፈሻ ዋሻ፣ የኃይል ማመንጫ ቤቱ፣ የዋሻ ቁፋሮና ተዛማጅ ሥራዎች ተጠናቀዋል።

254 ሜጋ ዋት የሚያመነጨውን ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በ451 ሚሊየን ዶላር ወጪ ግምባታው እየተከናወነ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት ተጠናቆ ሃይልማመንጨት ሲጀምር በአሁኑ ወቅት 4 ሺህ 260 ሜጋ ዋት የሆነውን የሀገሪቷን የሃይል አቅርቦት 4 ሺህ 514 ያደርሰዋል።

የግድቡ ግምባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ውሃ የመያዙ ስራ ከተከናወነ በኋላም ሃይል ወደ ማመንጨት ስራው የሚገባ መሆኑንም ነው አቶ ምስክር የተናገሩት።

የኃይል ማመንጫ ግድቡ ውሃ መያዝ የሚጀምር ሲሆን፥ ግደቡ 2 ነጥብ 57 ቢሊየን ኪዩ ቢክ ሜትር ውሃ ማጠራቀም እንደሚችል ነው የተገለፀው።

በ2003 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግድቡ ሲጠናቀቅ 110 ሜትር ከፍታ፣ 426 ሜትር ርዝመትና 98 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ይኖረዋል።

ኃይል ማመንጫው ለረጅም ዓመታት አገልግሎት መስጠት እንዲችልም የግንባታ ዲዛይን ለውጥ እንደተደረገለት ይታወሳል።

በተጨማሪም የረጲ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክትም አሁን ላይ ስራው 96 በመቶ ተጠናቆ በአሁኑ ወቅት የሃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግምባታም ተጠናቆ፤ የፍተሻ ስራዎች በመስራት ላይ ናቸው።

ምንጭ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *