( ታህሳስ 25 – 2010 )

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የዋናው ግድብ የኮንክሪት ሙሌት 9 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሲፈጸም፤ የሁለተኛው ፕሮጀክት የ’ሳድል ዳም’ ደግሞ 11 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የድንጋይ ሙሌት መከናወኑ ተገለጸ።

የግድቡን ግንባታ ሂደትና የደረሰበትን ደረጃ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የፕሮጀክቱ ኃላፊዎች በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስተባባሪነት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ገለፃ አድርገውላቸዋል።

በስፍራው የተገኙት ባለሞያዎችም የግድቡ ተቋራጭ ኩባንያዎች የሲቪልና የኤሌክትሮ ሃይድሮ መካኒካል ስራዎችን በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተመልክተዋል።

የዋናው ግድብ ቁመት ከባህር ወለል በላይ 145 ሜትር ከፍታ ሲኖረው፤ ወደ ጎን ደግሞ 1 ሺህ 780 ሜትር ርዝመት አለው።

በዚህ የግድቡ ከፍታ ላይ ለመድረስ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የአርማታ ሙሌት እንደሚያስፈልግ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ኃላፊ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ ግንባታ እየተሳተፈ ያለው የሰው ኃይል ቁጥር ከፍና ዝቅ የማለት ሁኔታ ይታይበታል ያሉት ኢንጂነር ስመኘው ቀደም ሲል የሰራተኞቹ ቁጥር 13 ሺህ ደርሶ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ዘጠኝ ሺህ ሰራተኞች በግንባታው ላይ እየተሳተፉ ነው ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ ከፍታ በጨመረ ቁጥር የግንባታው ስፋት እየጠበበ መሄዱ ለሰው ኃይልና ለማሽነሪዎች መቀነስ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

ከዋናው ግድብ ግርጌ የሚገኙት ሁለቱ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የኤሌክትሮ ሃይድሮ መካኒካልና የሲቪል ስራ እንዲሁም የድንገተኛና ከፍተኛ የውሃ ሙሌት ማስተንፈሻ በሮች ስራዎች በቅንጅትና በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

የ’ሳድል ዳም’ ግድብ 5 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 50 ሜትር ቁመት ያለው ሲሆን፤ ይህን 50 ሜትር ቁመት ከፍታ ለመሙላት 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የድንጋይ ሙሌት ያስፈልገዋል ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ አፈፃፀም 63 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *