(ታህሳስ 25 – 2010)

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በባቡር መስመር የመተሳሰር እቅድ እንዳላት ገለጸች።

ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ከመዲናዋ ካርቱም ዋድ ማዳኒ የተዘረጋውን የባቡር መስመር ስራ ትናንት መርቀዋል።

አል በሽር በምረቃ ስነ ስርዓቱ ወቅት እንዳሉት፥ ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በባቡር መስመር የመተሳሰር እቅድ አላት።

ከዚህ ባለፈም ከሌላኛዋ ጎረቤት ሃገር ደቡብ ሱዳን ጋር የሚያገናኝ የባቡር መስመር የመዘርጋት ፍላጎት መኖሩንም ገልጸዋል።

ወደ ደቡብ ሱዳን የሚዘረጋው የባቡር መስመር፥ ሃገራቸው ከኬንያና ኡጋንዳ ጋር ለምታደርገው የንግድ ልውውጥ መተላለፊያ በመሆን አጋዥ ይሆናልም ነው ያሉት።

ፕሬዚዳንቱ የባቡር መስመሮቹን የመዘርጋት እቅድ እንዳለ ከመግለጽ ውጭ፥ ፕሮጀክቶቹ ስለሚጀመሩበት ጊዜ ግን ያሉት ነገር የለም።

ሱዳን በርካታ ከተሞቿን በባቡር መስመር እንዳገናኘች መረጃዎች ያመላክታሉ።

ኢትዮጵያና ሱዳን በትራንስፖርት፣ በሃይል አቅርቦትና በቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፎች በትብብር ይሰራሉ።

ኢትዮጵያ እንደ ማዳበሪያ ያሉ ሸቀጦችን ለማስገባት የፖርት ሱዳን ወደብን ስትጠቀም፥ ሱዳን በበኩሏ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል በመግዛት ትገለገላለች።

በፈረንጆቹ 2016 ሃገራቱ በፀጥታ ዘርፎች በጋራ ለመስራትና ወታደራዊ ትብብራቸውን በማጠናከር ሽብርተኝነትን መከላከል የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

ባለፈው የካቲት ወር ደግሞ በተለያዩ መስኮች የሚያደርጉትን ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸውም የሚታወስ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *