(ህዳር 18፣ 2010)

ለረጅም ጊዜ ያለ አገልግሎት ተቀምጠው የነበሩት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አሳንሰሮች በሂደት ወደ ሥራ እንደሚገቡ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

በአሁኑ ጊዜም በአሳንሰሮቹ ላይ ፍተሸና የሙከራ ሥራ በመሰራት ላይ እንደሚገኝም ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።

የአዲስ አበባቀላል ባቡር ትራንዚት ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን አሰፋ በአዲስ አበባ ሰታዲዮም የሚገኘውን የቀላል ባቡር ጣቢያ አሳነሰር ፍተሸና የሙከራ ሥራ በአካል በመገኘት ተመልክተዋል።

አቶ ሙሉቀን አሰፋ እንደተናገሩት በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ጣቢያዎች ያሉ የአሳንሰር አገልግሎት ተገቢውን የደህንነት ፍተሻ እየተደረገላቸው እና መሥራታቸው እየተረጋገጠ በሂደት ወደ ሥራ እንደሚገቡ አስታውቀዋል።

በቀጣይም በእቅድ ተይዞ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚው በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ አሳንሱሮች በቅድሚያ ሥራ እንደሚጀምሩ ገልፀዋል።

በእስጢፋኖስ፣ በሜክሲኮ፣ በለገሃር፣ በመገናኛ፣ በምኒሊክ አደባባይ ሚገኙ አሳንሰሮች በቀጣይ በሚደረግ የፍተሸ እና የሙከራ ማረጋገጫ ወደ ሥራ የሚገቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የአሳንሰሮቹ አገልግሎት ለጊዜው ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት እንደሚሆን አቶ አወቀ አሰፋ የተናገሩ ሲሆን፥ በሂደትም ሰው የሚበዛበት ቦታ እየታየ የአቅመ ደካሞችን እና የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎችን እንቅስቃሴ በማይገድብ መልኩ የአገልግሎት ሰዓቱ እንደሚረዛም አመላክተዋል።

የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ያለምንም ችግር በአሳንሰሮቹ እንዲገለገሉባቸው እና የደህንነትም ችግር እንዳይፈጠር የሰለጠኑ ባለሙያዎች በየባቡር ጣቢያው ባሉ አሳንሰሮች ድጋፍ የሚደርግ የሰው ኃይል ያዘጋጀ መዘጋጀቱንም ሃላፊው ጠቅሰዋል።

በተያያዘ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጥ የቆየውን የልደታ ባቡር ጣቢያም በሚቀጥሉት 21 ቀናት ውስጥ ሥራ ሊጀምሩ እንደሚችሉ አቶ አወቀ ተናግረዋል።

የባቡር ጣቢያን ወደ ሥራ ለማስገባት ያለው ሂደት የተጀመረ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፥ በአካባቢው ከሚገኘው የህንጻ ባለቤት ጋር በደህንነት ድንበር አወሳሰን፣ የመብራት አጠቃቀም እና የህንጻውን በሮች በምን መልኩ እንደሚጋሩ እና በሌሎች ተዛማች ጉዳዮች ላይ ውል ለመፈራረም በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

አዲስ አበባ ቀላል ባቡር ካሉት 39 ፌርማታዎች ዘጠኙ በከፍታ ድልድዮች ላይ አንዱ ደግሞ በዋሻ ውስጥ ይገኛሉ።

እነዚህን ፌርማታዎች ተደራሽ ለማድረግ አሳንሰሮች ቢተከሉም አገልግሎት ሳይሰጡ ሁለት ዓመታት መቆጠራቸውን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል።

ምንጭ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *