(ኢዜአ)- የማዕከሉ ኃላፊ ተወካይና የአዞ ልማት ባለሙያ ወይዘሪት እህት በቀለ እንደገለፁት ማዕከሉ ቀደም ሲል የሚሰጠውን አገልግሎት ከቱሪዝም ዘርፍ ጋር ብቻ  በማያያዝ በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ስር እንዲተዳደር ተደርጎ ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት  የስጋ ምርትን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የነበረው እቅድ ሳይሳካ መቆየቱን ጠቅሰው  ካለፈው ዓመት ጀምሮ በእንስሳትና አሳ ሀብት ልማት ቢሮ ስር መተዳደር በመጀመሩ እቅዱ እንዲሳካ መንገድ መክፈቱን አመልክተዋል፡፡

አሁን ማዕከሉ ስጋውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተዘጋጀ ያለው ቀደም ሲል እየላከ ካለው  የአዞ ቆዳ በተጨማሪ ነው።

ለዚሁ ተግባር ከ2005 ዓ.ም በግንባታ ላይ የነበረው የአዞ እርድ ቄራና የጫጩት ማሳደጊያ ገንዳ ተጠናቆ ለአገልግሎት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

“የእርድ ቄራው አስፈላጊው ቁሳቁስ ተሟልቶለት በቅርቡ ስራ ይጀምራል ” ብለዋል።

ከአባያና ጫሞ ሐይቆች ተሰብስበው በማዕከሉ በማደግ ላይ ከነበሩ 4ሺህ 546 አዞች መካከል 2ሺህ የሚሆኑት ለእርድ ደርሰዋል፡፡

እንደ ወይዘሪት እህት ገለፃ የደረሱ  የአዞ ስጋ ለመረከብ ናሙና ከወሰዱ የተለያዩ ሀገራት ጋር ድርድር እየተደረገ ነው ።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትከ ጃፓንና ቻይና የመጡ ባለሀብቶች ከቆዳ በተጨማሪ ስጋ ለመረከብ ናሙና መውሰዳቸውን ጠቅሰው  ምርቱም ወደ ሀገራቱ የሚላክ መሆኑን አመላክተዋል።

አንድ የደረሰ የአዞ ቆዳ በዓለም ገበያ ከ350 እስከ 400 ዶላር እንዲሁም ምርቱን ለመቀበል ፍላጎት ባሳዩ ሀገራት አንድ ኪሎ የአዞ ስጋ 160 ዶላር ዋጋ እንደሚያወጣ ነው ተወካያዋ የጠቆሙት።

የገበያ ድርድሩ ከተሳካ በበጀት ዓመቱ ከቆዳና ስጋ ምርት ሽያጭ እስከ 800 ሺህ ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ታቅዷል፡፡

“እድሜው ከስድስት ዓመት ያልበለጠ አንድ ለእርድ የደረሰ አዞ ከ5 እስከ 6 ኪሎ ግራም የሚመዝን ስጋ አለው፤ ከስጋ ሽያጭ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንደሚገኝ በጥናት ተረጋግጧል ” ብለዋል ።

 ማዕከሉ ከቆዳና ሌሎች ተረፈ ምርቶች ሽያጭ ከሚያስገኘው ምንዛሪ በተጨማሪ ከጎብኝዎች የሚሰበስበው የገቢ መጠን እያደገ መምጣቱን የገለፁት ደግሞ የማዕከሉ አስጎብኚ ወይዘሪት ህይወት አሰፋ ናቸው ።

በ2009 በጀት ዓመት መጨረሻ ባሉት ሶስት ወራት ብቻ ማዕከሉን ከጎበኙ ከ162 የውጭ  ጎብኝዎች 1ሺህ 620 ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል ።

እንደ ወይዘሪት ህይወት ገለፃ በዚሁ ጊዜ ከ8ሺህ  የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች የአዞ እርበታ ማዕከሉን ተመልክተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *